እናት ፓርቲ

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ መግለጫ የሰጠው እናት ፓርቲ የሚከተለውን ብሏል:_

ሀገር ፈርሳ ተቅበዝባዥ ከመሆናችን በፊት ኹሉም ለሀልዎቷ ዘብ ይቁም!

ሃይማኖተኝነት የሚያስከበር ጸጋ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ የቆዩና ዘለግ ያለ ታሪክ ያላቸው ሀገራት ደግሞ እንዲህ ያለ እሴታቸው እየተጠናና እየተሰነደ ለዓለም ትምህርት ወዲህም ሀብት የሚሆን ጸጋ እንደሆነ ብዙ ሀገራትን እንደምሣሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

የእኛን ለየት የሚያደርገው በአንድ ገጽ ብቻ የሚነበብ ሳይሆን በተለይ በኹለቱ ቤተእምነቶችና ምዕመናን ዘንድ ያለ፣ የነበረና የሚኖር መከባበርና መፋቀር፣ ጥልቅ የሰዋዊና ሥነምግባር አስተምህሮቶች፣ አብረሃማዊ መሠረቶችን አጽንቶ የማቆየትና የማስቀጠል ልማድ በልዩነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

አኹን አኹን በእነግብጽ፣ አልሸባብና መሰሎቻቸው ረጂም እጆች፣ ወዲህም ደግሞ ትሕነግ፣ በሕጋዊ እና ሃይማኖተኝነት ጭንብል የሚንቀሳቀሱ መሰል የቅርብ ግን ደግሞ የጭቃ ውስጥ እሾኮች አንዳንዴም ከሃይማኖት አባቶች ተግሳጽ መጓደል በአደገኛ ኹኔታ እየተሸረሸረ ጭራሽ ሀገርን ወደከባድ አዘቅት ለመወርወር እያኮበኮበ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ለሉላዊነት ሴኩላሪዝም እንቅፋት ይሆንብናል ብለው የሚያስቡ የምዕራቡ ዓለም ስልት ቀያሾችና ሀሳዊ መንገድ ጠራጊዎች የጥቃቱን ግንባር እየቀያየሩ መሞከራቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡

በሀገራችን ላይ እስከአኹን የተሰነዘሩ ቀስቶች ፍቅርና አንድነት አንዳንዴም ችሎ ማለፍ በሚባሉ ጋሻዎች ተመክተዋል፡፡

የአኹኑ ጥቂት የሚለየው ከኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የራሳቸውን ሕልውና ለማጽናት የሚታትሩ ኃይሎች “ተገፍተህ፣ ተጨቁነህ” ብለው ቤንዚኑን በሀገር ውስጥ ጥቅመኞቻቸው አማካይነት እያርከፈከፉ እሳቱን ይበልጥ የሚያቀጣጥሉበት፣ አብዛኛው በዚሁ ሥነልቡና የሚሰቃይበት አለፍ ሲልም ለበቀል ቢላ የሚስለበት፣ ተው ባይ የጠፋበት/አፉን የሸበበበት፣ መንግስት ዐቢይ ሚናውን የረሳበት/የተወበት፣ ልሂቁም አሞራ በሰማይ የሚያወራበት ጊዜ መኾኑ ነው፡፡

ይህም አጠቃላይ ለኩነቱ የሰመረ መደላድል ሳይሆንለት አልቀረም፣ አይቀርም፡፡ ቁምነገሩ በሃይማኖትም ይምጣ በጎሳ፣ ቱርክ ይጠንሰስ፣ ግብጽ ይቦካ፣ አሜሪካ ይጋገር የድግሱ የመጨረሻ ግብ የኢትዮጵያን የቁልቁለት ጉዞ ማፍጠን ብሎም ማፍረስ ነው፡፡

እናት ፓርቲ የሰሞኑን የጥፋት ድግስ በቅርበት ሲከታተለው የነበረ ሲሆን ባሰባሰብነው መረጃና ማስረጃም ጉዳዩ ለሀገር አንድነት የሚቆሙ የሃይማኖት ተቋማትን በማፍረስ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ እንጂ ሃይማኖታዊ ግጭት አለመሆኑን ተረድተናል፡፡

ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በጥንታዊቷና ተፋቅሮ መኖርን በምታስተምረው ጎንደር ከተማ በተነሳ ግጭት ሰዎች ሞተዋል፣ ንብረት ወድሟል፤ በዚህም እናት ፓርቲ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ለመግለጽ ይወዳል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ ጉዳይን በውል በማይረዱ፣ ወዲህም በዓላማ ጭምር መንግስታዊ መዋቅርን ለጥፋት ተልዕኮ በሚጠቀሙ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አክራሪዎች የእልቂት ድግስ ቅስቀሳዎች፣ ከፍተኛ መናበብና የቀደመ ዝግጅት መኖሩን በሚያረጋግጥ መልኩ በማግስቱ ስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማና አካባቢው አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለዋል፣ ምዕመናን በግፍ ተገድለዋል፡፡

እንዲሁ በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ጅግጅጋ የሴራው ጭስ የታየ ቢሆንም በክርስቲያኑም ሙስሊሙም ትብብር ከስሟል፡፡

ክስተቱ ግን የመጪው ጊዜያት የሀገራችንን እጣ ፈንታ ፍንትው አድርጎ ያሳዬ ሆኗል፡፡ በዚህ አጋጣሚ እናት ፓርቲ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ለመግለጽ ይወዳል፡፡

በዚህ የጥፋት ዘመቻ ወቅት በጎንደርና ወራቤ ከተማ ጥቃት የተሰነዘረባቸው ወገኖች ሲሳደዱ በየቤታቸው አስገብተው ከጥቃት የመታደግ ሥራ በመሥራት ኢትዮጵያዊ ከፍታቸውን በመከራ ወቅት ላሳዩ ወገኖቻችን ያለንን ታላቅ አክብሮትና ምሥጋና ለመግለጽ እንወዳለን።

በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ ጊዶሌ ከተማና አካባቢው በዚሁ ሰሞን የጠየቅነውና ቃል የተገባልን ለምን አይፈጸምም? በሚል መነሻና በአስተዳደሩ እንዝህላልነት ችግር ተከስቶ ቀላል የማይባል የሰው ሕይወት እንደጠፋ፣ ንብረት እንደወደመ ለመረዳት ችለናል፡፡

ይህም ሀዘናችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡ በአጠቃላይ እናት ፓርቲ በእነዚህና መሰል አኹናዊ ቀውሶች ዙሪያ ቀጣዮቹን የመፍትሔ ጥቆማዎችና ማሳሰቢያዎችን ለማቅረብ ይወዳል፡-

፩. የሰሞኑ ክስተት ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ይምሰል እንጂ በጥንቃቄ የተቀናበረና ዓላማውም ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ መሆኑን ተረድቶ ኹሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ከጥፋት ጠንሳሾች ሴራ ለመታደግ ያለማንም ቀስቃሽ ዘብ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡

፪. መንግስት እንደ ተቋምና በባለስልጣናቱ በኩል በንግግርም በተግባርም በሃይማኖት ተቋማት መሐል በሚፈጠር ግጭት ፖለቲካዊ ትርፍ የማትረፍ አዝማሚያውን በአፋጣኝ እንዲያቆም እናሳስባለን፡፡

፫. ለግጭት ሰበብ የሚሆኑና መደላድል የሚፈጥሩ ምክንያቶችን በአብያተ እምነቱ ሊቃውንት በኩል በውል ተጠንተው ባዳበሩት ፍልስፍናና ችግር መፍቻ ዘዬ ተመክሮና ተዘክሮ ችግሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ የሚያገኝበትን ፍኖት እንዲተልሙ እንጠይቃለን፡፡

፫. በሰሞኑ ግጭት የተሳተፉ፣ ያባባሱ፣ የእልቂት አዋጅ ነጋሪዎች፣ ባለስልጣናት፣ ተቋማትና የመገናኛ ብዙኃን በውል ተጣርቶ በሕግ ፊት እንዲቀርቡ አበክረን እንጠይቃለን፡፡

፬. ትናንት ሀገር ምጥ ውስጥ በገባችበት አጋጣሚ “ድረስልን” ተብሎ ቤትና ንብረቱን እየሸጠ ዘምቶ ለሕልውናችን ዋጋ የከፈለውን “ፋኖ” ቢቻል ማመስገን ሲገባ በተቀናበረ መንገድ መወንጀል እና ያለ ግብሩ የጦስ ዶሮ ለማድረግ የተኬደበት ርቀት አግባብ ባለመሆኑ አንዳንድ አካላት ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እንጠይቃለን፡፡

፭. ደራሼና መሰል የመዋቅር ጥያቄ ያላቸው አካባቢዎች የምርጫ ካርድ ለማግኘት ሲባል አጓጉል ቃል በመግባት ሳይሆን ጥያቄዎቹ ሕግንና ሕግን ተከትሎ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ ብሎም የአካባቢው አስተዳደር ሰላማዊ ጥያቆዎችን በአፈሙዝ ከማስተናገድ እንዲቆጠብ በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡

እናት ፓርቲ በእነዚህና መሰል አካባቢዎች በግጭቱ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ይመኛል፤ የተጎዱትን በማቋቋሙ ሂደትም የበኩሉን እንደሚወጣ ቃል ይገባል፡፡

By Admin

Amhara elites must be militant democrat to stop anti democratic fascism act on our people by those extremist nationalists(TPLF ,OLF), and also name covered prosperity,EPRDF. ትንሳኤ አማራ በልጆቹ ትግል እውን ይሆናል።

Translator