★ ሙሴን ፣ ዳዊትን ጠቢቡ ሰሎሞንን ያፈራው የአይሁድ ህዝብ በመጀመሪያው ክ/ዘመን መባቻ አካባቢ ሙሉበሙሉ ብቻውን ነበር ማለት ይቻላል ። የአይሁድ ህዝብ የአለማችን ጥበብ ፣ ታሪክ ፣ ሐይማኖት መነሻ ምንጭ ያደረጉት ልጆች እንዳልነበረው ሁሉ በሮማውያን ቅኝ ግዛት ስር የወደቀበትና በኃያሉ ቅዱስ ዳዊት ከተማ ላይ እንደ ብአዴናዊያን አይነት ሙጃወች የበቀሉበት ዘመን ነበር ።
★ ይስማዕከ ወርቁ በመፅሃፉ ” ፋሲል በተጠበበት ፣ ቴወድሮስ ታሪክ በሰራበት እናንተ ተወለዳችሁበት ። ከእናንተም ብሶ ትናናቃላችሁ ። እናንተ ማለት እኮ በፋሲል ቤተመንግስት ላይ የበቀላችሁ ሙጃወች ናችሁ ” እንዳለው በኃያሉ ዳዊትና በጠቢቡ ሰሎሞን ከተማ ላይ የሮማውያንን ቅኝ ግዛት አስተዳደር እንደራሴ የነበሩት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የሮም መንግሥት በሐገራቸው ላይ በፈቀደላቸው ስልጣንና ሀብት ደልቷቸው ይኖሩ ነበር ።
★ የትህነግ እንደራሴ ሆኖ አማራን ትናንት “ዋነኛው ጠላታችን ድህነት ነው ፣ የተጀመረውን ድህነትን የማሸነፍ ጉዞ ለማስቀጠልና ከዳር ለማድረስ ” እያለ የህዝባችን የነፃነትና ሉዓላዊነት ፍላጎት በማፈን ለ 27 አመት የወያኔ የቅኝ አገዛዝ አስፈፃሚ የነበረውና ዛሬ ደግሞ ሎሌነቱንና እንደራሴነቱን ከትህነግ ወደ ኦነግ በመቀየር መሬት ከምትሽከረከርበት ምህዋር ብትደናቀፍ በአለም ላይ ሊከሰት ከሚችለው መቅሰፍት ማመሳሰል ብቻ በቀረው ” ለውጡ እንዳይደናቀፍ ፣ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ከዳር ለማድረስ ፣ ለውጡ እንዳይቀለበስ” በሚል ስብከት የኦሮሙማ መንግሥት የቅኝ ግዛት ቀንበርን በህዝባችን ላይ የመጫን ተልዕኮውን እየተወጣ እንዳለው ብአዴን ፤ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያኑም በሮም መንግሥት ለተቸራቸው ስልጣንና ሀብት ሲሉ የሮም መንግሥትን የቅኝ ግዛት ቀንበር እና የጭቆና አገዛዝ በመቃወም በሮም መንግሥት ላይ የሚነሳ የትኛውም አይነት ተቃውሞና አመፅን በማውገዝ በሮም መንግሥት አገዛዝ ስር በሰላም እንዴት መኖር እንደሚቻል ” ፖክስ ሮማ” ( የሮማ ሰላም) የሚባል አጀንዳን ያራምዱና ይሰብኩ ነበር ።
★ ነገር ግን ይህ ” የፖክስ ሮማ” ስብከት ለአይሁድ ህዝብ ከተጫነበት የቅኝ ግዛት ቀንበር የሚያላቅቀውና የወደቀበትን ከባድ የጭቆና አገዛዝ የሚያቀልለለት ስላልነበረ በተራው ህዝ ዘንድ የተፈጠረው የለውጥና የነፃነት ፍላጎት አይሎ “በሰላም መገዛትን እንፈልጋለን ” በሚለው የፈሪሳውያኑና ሰዱቃውያኑ ጎራ እና ” ነፃነት ወይም ሞት ” በሚለው የአማፂው ጎራ መካከል አደባባይ ነውጥ እና ወደ ከባድ ግጭት አመራ ። ” ነፃነት ወይም ሞት ብሎ የተነሳው የአማፂው ጎራ ራሱን በህቡዕ እያደራጀ እየታጠቀ የፈሪሳውያንና ሰዱቃውያኑን ባለስልጣናት ማጥቃት እና የሮም መንግሥት ደጋፊ ናቸው የሚሏቸውን ባለሀብቶች ንበረት ማውደምና መዝረፍ ጀመረ ።
★ በመቀጠል ፀረ ቅኝ አገዛዝ አመፁ ተጠናክሮና አድጎ የተደራጀና ቤን ያኢር የሚባል መሪ ያለው ተዋጊ ሀይል ለማቋቋም ቻለ ። ይህ የተቋቋመው የአይሁድ ነፃ አውጭወች ታጣቂ ሀይል በሮም መንግሥት ሰራዊት ላይ በልዩልዩ ቦታወች አደጋ በመጣል ማጥቃት ጀመረ ። የትጥቅ ትግሉን አጠናክሮ ሙት ባህር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የነበረውንና ብዙ የጦር መሳሪያ ተከማችቶ የሚገኝበትን የሮም መንግሥት የጦር ሰፈር በማጥቃት ሰራዊቱን ከደመሰሰ በሗላ የተከማቸውን የጦር መሳሪያ በሙሉ ወስዶ ታጠቀ ።
★ የዚህ ነፃ አውጭ ታጣቂ ሀይል ዝና በመላው አይሁድ ዘንድ በመሰማቱ በእየሩሳሌምና በሮም ቅኝ ግዛት ስር በነበሩ በሌሎች አጎራባች ሀገሮች ፀረ ሮም አመፅ እንዲቀሰቀስ አደረ ።
★ በመቀጠል ሀይሉን አጠናክሮ በጫካ የደፈጣ ውጊያ ሳይወሰን በእየሩሳሌም ከተማ የሚገኘውን የሮም መንግሥት ሰራዊት በመደምሰስ እየሩሳሌምን መቆጣጠር ቻለ ።
★ የእየሩሳሌም በአማፂ ሀይሉ እጅ መውደቅ እና ከእስራኤል አልፎ በጎረቤት የሮም መንግሥት የቅኝ ግዛቶች እየተቀጣጠለ የመጣው ፀረ ሮም አመፅና ንቅናቄ የሮምን መንግሥት ትልቅ ስጋት ውስጥ ከተተው ።
★ በመሆኑም በአፋጣኝ እየሩሳሌምን ከአማፂ ሀይሉ እጅ ለማውጣትና አማፂ ሀይሉንም በአፋጣኝ ለመደምሰስ ከሮምና ከእስራኤል አጎራባቾች የተውጣጣ ከ 50, 000 በላይ ወታደሮቹን ሴስቲየስ ጋላስ በተባለው ጀነራሉ መሪነት አንቀሳቀሰ። ነገር ግን አማፂ ሀይሉ እየሩሳሌምን እንደተቆጣጠረ ከነባር ታጋዮቹ በተጨማሪ 24,000 የሚጠጉ አይሁዳውያንን ጭምር በእየሩሳሌም በዙሪያዋ ሁሉ አሰልፎ ነበር ። አማፂው እየሩሳሌምን እየንደተቆጣጠረ ሁሉም የአይሁድ ህዝብ ወታደር ሆኖ ነበር ። ሁሉም ከአማፂው ጎን ተሰልፎ እየተዋጋ ነበር ።
★ ሴስቲየስ ጋላስ በተባለው ጀነራል የሚመራው የሮም መንግሥት ጦር ለ 5 ቀናት እየሩሳሌምን ከቦ ከተዋጋ በሗላ አንበሳ እንደተቆጣ አይታደንም የሚባለውን ጥበብ በመጠቀም በድንገት እንዲያፈገፍግና የተሸነፈ በመምሰል የይሁዳን ምድር ለቆ እንዲወጣ ተደረገ ።
☞ እዚ ጋ በአለማችን የጦርነት ታሪኮች ውስጥ ከትሮይ ጦርነት ታሪክ የማይተናነስ ትልቅ አስማት ተሰራ ።
★ የሮም መንግሥት እንደራሴ ሆነው ህዝባቸውን ለሮማ ቄሳር ሲያስገብሩ የነበሩት ሰዱቃውያኑና ፈሪሳውያኑ የንጋት አርበኞች ሆነው ብቅ አሉ ። የቄሳርን የቅኝ ግዛት ቀንበር ሰብረነዋል ፣ የሮም መንግሥት የበላይነትና ቅኝ ገዥነቱም ላይመለስ ተቀብሯል ፣ የአይሁድ ህዝብ ከእንግዲህ ወደ ሰላማዊ ኑሮው መመለስ አለበት ፣ ከእንግዲህ ጦርነት የለም ፣ የአማፂ ሀይሉ አባላትም ከጫካ የትጥቅ ትግላቸው ወጥተው ወደ ከተሞቻቸውና ኑሯቸው ይመለሱ በማለት የአይሁድን ህዝብ መልሶ የማስተኛት ስብከታቸውን በአራቱም የይሁዳ ምድር አቅጣጫዎች በማናፈስ የህዝቡን የጋለ የትግል መንፈስ በማቀዝቀዝ ከአማፂ ሀይሉ ጎን ተሰልፎ የሮም መንግሥትን ጦር እንዳይመክትና ሐገሩን እንዳይጠብቅ ታላቅና ታሪካዊ ሸፍጥ ፈፀሙ ።
★ በመሆኑም በሮማ ሰራዊት የተሸነፈ በመምሰል እየሩሳሌምን ለቆ መውጣት እና በፈሪሳውያኑ የሸፍጥ ስብከት የአይሁድ ህዝብ አስተሳሰብ ለሁለት ተከፈለ ። ብዙሀኑ ህዝብም የሸፍጠኞቹን ስብከት ተቀብሎ ከየምሽጉና ግንባሩ እየወጣ ወደ ሰላማዊ ኑሮው መመለስን መረጠ ።
★ ጥቂቶቹና ቆራጦቹ የአማፂ ሀይሉ አባላት ደግሞ ” የነብርን ጅራት አይዙም ከያዙም አይለቁም “ እንደሚባለው የሮም መንግሥት ጦር የተሸነፈ በመምሰል ስልታዊ ማፈግፈግ ማድረጉንና አመች ጊዜ ጠብቆ ተመልሶ እንደሚመጣ ጠንቅቀው በመረዳታቸው ለጊዜው የተቆጣጠሯትን እየሩሳሌምን ለቀው ወደ በረሃቸው ለመሄድ ወሰኑ ።
★ የእነዚህ ቆራጥ አርበኞች መሪ ቤኒ ያኢርም በእየሩሳሌም አደባባይ ላይ ለአይሁድ ህዝብ ሁሉ እንዲህ የሚል ንግግር አደረገ ፦
☞ ” ጀግኖች ወገኖቼ ሆይ ከእንግዲህ ከአምላክ በስተቀር ለሮማውያኑም ሆነ ለማንም ሰው ባሪያ አንሆንም ። እጃችን ሰይፍ መጨበጥ እስከቻለ ድረስ ኑ ። ተመልሰን የጠላቶቻችን ባሪያ ከመሆናችን በፊት እንሙት ። ይህን ህይወታችን ከሚስቶቻችንና ልጆቻችን ጋ ነፃ ሰወች እያለን ትተነው እንሂድ ።”
★ ነገር ግን የፈሪሳውያኑና ሰዱቃውያኑ የሸፍጥ ስብከት በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲያንቀላፋ የተደረገው የአይሁድ ህዝብ መስማት አልቻለም ። ” ለውጡ እንዳይደናቀፍ ፣ እንዳይቀለበስ ” እንደሚለው ብአዴናዊ ስብከት ሁሉ ” የሮም መንግሥት ከእንግዲህ ላይመለስ ተሸኝቷል ” የሚለው የፈሪሳውያኑና ሰዱቃውያኑ ስብከትም ” የአይሁድ ህዝብ ከአማፂያኑ ጎን ተሰልፎ ወደ ጫካ የሚወርድና ወታደርነቱን የሚያጠናክር ከሆነ የሮም መንግሥት የእስራኤል አጎራባች የሆኑ ቅኝ ግዛቶቹ ላይ ወረራ ይፈፅሙብኛል በሚል ስጋት ተመልሶ በመምጣት ይዋጋናል ። ስለሆነም የአይሁድ ህዝብ ከእንግዲህ የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ ፣ አይሁዳውያኑ ከአማፂ ሀይሉ ጎን ተሰልፈው የሚያደርጉት የጦርነት ዝግጅትና ስልጠና ስጋት ሆኖበት የሮም መንግሥት ጦሩን እንዳያዘምትብን ሁሉም ወደ ሰላማዊ ኑሮው ይግባ በሚል ስር የተጠናከረ በመሆኑ ለአመታት በአርበኝነት በረሃ የኖሩ የአማፂ ሀይሉ አባላትንም በእየሩሳሌም እንዲቀሩ አደረጋቸው ።
★ የቤኒአሚር ታማኞች የሆኑ ጥቂቶች ብቻ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ጭምር አስከትለው ወደ በረሃ በመግባት ማሳድ በተባለው ምሽጋቸው ተቀመጡ ።
★ አንበሳ እንደተቆጣ አይታደንም በሚል መርህ ያፈገፈገው የሮም መንግሥት ከአራት አመት በሗላ በ70 አ.ም እስራኤላዊያን የማለፍ በዓላቸውን ለማክበር በእየሩሳሌም በተሰባሰቡበት ወቅት የአይሁዳውያንን አመፅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆምና ለመደምሰስ በጀነራል ቲቶ የሚመራ አራት ክፍለ ጦሩን በማዝመት እየሩሳሌምን ከበበ ።
★ በእስራኤል ከሚኖሩት በተጨማሪ በመላው የሮም ግዛት ስር የሚኖሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አይሁዶች በዓሉን ለማክበር ወደ እየሩሳሌም ገብተው ነበር ። በመሆኑም መላው የአይሁድ ህዝብ ለማምለጥ ከማይችልበት የመጨረሻው የከበባ ወጥመድ ውስጥ ገባ ።
★ የሮም መንግሥት ጦርም የይሁዳን ምድር በመላ እንዳልነበረች አደረጋት ። ከ 1 ሚሊዮን በላይ አይሁዶች ተገደሉ ። ከግማሽ ሚሊዮን የማያንሱት ደግሞ በምርኮ ተይዘው ወደ ልዩልዩ የሮም ግዛቶች ሲወሰዱ በደረሰባቸው መከራና እንግልት በጉዞ ላይ እንዳሉ ረገፉ ።
★ የሮም መንግሥት ጦር የይሁዳን ምድር እንዳልነበረች ካደረገ በሗላ በረሃ ያሉትን የአማፂ ሀይሎች ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ከሁሉም አቅጣጫ ወደ አማፂያኑ የማሳድ ምሽግ ተንቀሳቀሰ ።
★ የአማፂያኑን ምሽግ በተጠናከረ ቀለበት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ውጊያ በማድረግ ምሽጉን ሰብሮ ለመግባት ተቃረበ ።
★ የምሽጉ መሰበርና የአማፂያኑ በሮም መንግሥት ጦር እጅ መውደቅ ቁርጥ ሆነ ።
★ ነገር ግን የሮም ሰራዊቶች ምሽጉን ሰብረው ለመግባት በተቃረቡበት ወቅት የአማፂ ሀይሉ አባላት ” በጠላት እጅ ከምንወድቅ ራሳችን በራሳችን እናጥፋ የሚል ውሳኔ ላይ ደረሱ ። በመሆኑም ሁሉም በአንድ ላይ ቤተሰባቸውን ከገደሉ በሗላ የቀሩትን የሚገድሉ አስር ሰወች እጣ ተጣጣሉ ። እያንዳንዱ ሰውም በሚስቱና በልጆቹ ላይ እጁን ከዘረጋ በሗላ እያንዳንዳቸው በተመሳሳይ መንገድ እርስበእርስ ተገዳደሉ ። ይህን በሚመስል አሰቃቂ ሁኔታ በምሽጉ ውስጥ የነበሩ ከ 1000 በላይ የሚሆኑ አርበኞችና ቤተሰቦቻቸው አለቁ ።
★ ሮማውያኑ ምሽጉን ሰብረው ሲገቡ ከሁለት አቅመ ደካማ ሴቶች ውጭ በህይወት ያገኙት ሰው አልነበረም ።
★ በዚህ ከትሮይ ጦርነት አስማት በማይተናነስ የሮም መንግሥት ጦር ማፈግፈግና የተሸነፈ በመምሰል እየሩሳሌምን ለቆ እንዲወጣ መደረግ እየሩሳሌም የትሮይ ከተማን እጣ ፋንታ እንዲገጥማትና በጊዜው ከሞት መትረፍ የቻለው የአይሁድ ህዝብ ደግሞ ለ2000 አመት ገደማ በአለም ተበትኖ አገር አልባ ፣ ነፃነት አልባ የሆነ ስደተኛ ህዝብ ሆኖ እንዲኖር ተደርጓል ።
★ የትሮይ ከተማና ህዝቦቿ የጠፉት ከግሪክ ጋ ለ 10 አመታት ባደረጉት እልህ አስጨረሽ ጦርነት ምክንያት ሳይሆን ግሪኮች ተሸንፈው ሄደዋል በማለት ተዘናግተው በተኙባት በዛች በአንዷ ሌሊት ምክንያት ነበር ።
★ በመሆኑም የአማራ ህዝብ የራሱ ውድቀትና ጥፋት ከመምጣቱ በፊት ከሌሎች ውድቀትና ጥፋት መማር አለበት!!!
★ እንግዲህ ሰላምን የፈለገ ህዝብ ቢኖር ሰላምን ለመጠበቅ አስፈላጊ ለሆነው ጦርነት ይዘጋጅ ፣
ህልውናውን ለማስቀጠል የሚፈልግ ህዝብ ቢኖር ህልውናውን ለማስቀጠል የሚበጀውን ሞት ለመሞት የተዘጋጀ ይሁን እያልኩኝ ፤
ታሪካዊ በሆነው የአይሁዳውያን አማፂ ሀይሎች መሪ በቤኒያሚር የእየሩሳሌም አደባባይ ንግግር ልጨርስ ፦
☞ ” ጀግኖች ወገኖቼ ሆይ ከእንግዲህ ከአምላክ በስተቀር ለሮማውያኑም ሆነ ለማንም ሰው ባሪያ አንሆንም ። እጃችን ሰይፍ መጨበጥ እስከቻለ ድረስ ኑ ። ተመልሰን የጠላቶቻችን ባሪያ ከመሆናችን በፊት እንሙት ። ይህን ህይወታችን ከሚስቶቻችንና ልጆቻችን ጋ ነፃ ሰወች እያለን ትተነው እንሂድ ።” !!!
የበረራዋ ወንጌል
Read Time:6 Minute, 0 Second